Amharic poem (አማረኛ ግጥም)


ሀገሬ 

ሀገሬ ዳገትሽን በዳዴ ልለፈው
አሜካላሽ በዛ ምኑን ልደገፈው
 የከሸፈ ትውልድ ሁሉም ታሞ ታሞ 
ውሻ ያስከትላል ቆዳ ተሸክሞ
አየው አየውና እንዳልተፈረደ
ጅቡን ይቀልባል በጉን እያረደ።



    አሯሯጭ 

እዚያ ጋ ወደ ዛ

ምንድን ነው ሰው በዛ 

የለለ ነው ሙዱ 

ከእነርሱ መሄዱ 

ሩጡ ተሮጠ

ጩኸት ተቀወጠ
በሉ እዚ እንጀምር
አንተኛው ተገር
እነዚያን ተሳደብ እነሱን አወድስ
ትንሽ ታሪክ ተርክ ጀግና ጎሳ ጥቀስ
አንተ በል አንተ በል አንተኛው ተጣራ
አንተ ደግሞ አንተኛው በል ደንጋይ ወርውራ
ዛሬማ እንቀውጠው ድምፃችን ይሠማ
መብራቱን እናጥፍው እናርገው ጨለማ
ክበብ ከተራራ መንገዱ ይዘጋ
እጃችን ወደ ላይ ከፍ ይበል ይዘርጋ
እኮ በዚያ ሠፈር በዚያ ሠፈር እማ
ዛሬ አንድ ሰልፍ አለ ነገ ደግሞ አንድ አድማ
አኮ ! ለምንድን ነው ቀዘቀዘ እኛ ጋ
በል ተነሥ ወገኔ ፍጠን እንዋጋ
ሥማማ ወንድሜ ይኸም ኑሮ ተብሎ
ይሻላል ወይን ቤት መግባት አንዱን ገሎ
አልሠማህም እንዴ በዚያ በአሜሪካ
ብለህ ከአመለከትክ መብቴ ተነካ
Sorry men ተብለህ ይሰጥሀል ካሳ
እውነት እንድጠብቅ ህግን እንዳትረሳ
ይህንን ጥያቄ እዚህ ብታነሳ
አጥንትህ ለውሻ ሥጋህን ለአንበሳ
በሆድ በአንጀት ብሎ
ለማለፍ አታሎ
እንደዚህ እያለ መርዙን እየረጨ
እርሱ ይጋግራል ሯጭ እያስፈጨ
ጀግናው! እኔ እምልህ
ልቅደም ትቀድማለህ
ችግር የለም ልቅደም
አንተ ከምትደክም
እንዴ ! አንተ ወንድ አይደለህ እያለ አሥጀምሮ
ወደ ጠብ ሲአመራ ያ አድማ ጠንክሮ
አይ አሮሯጭ ወንዱ ከዳር ይቀመጣል ማልያ ቀይሮ።


እውነት ገደል ይግባ 
በትክክል ሀሳብ ከእውነት ተነሥቸ 
አገር ወገን ይስማ ብዬ ተገዝቸ 
ክስ ተካሰሸ ሙግት ተሟግቸ 
እንዲጠበቅ ክብሬ ጠበቃ ገትሬ
 ስሟገት ወጥሬ
 ዳኛው ለእኔ ፈርዶ 
ስለእውነት ተገዶ 
ከአለቀ በኋላ ፍርዴን ተቀብዬ
 ይባስ እስር ገባው ጠንክሮ ስቃዬ
 የብስራቴ ድግስ የድሉ እጅ መንሻ 
ሂድ ይሉኝ ጀመረ እንደ አሮጌ ውሻ 
የደከመ የአልኩት ሆኖብኝ አንበሳ 
ቀን ሲጨልምብኝ ሥጓዝ በዳሠሳ 
ሽንፈትን መረጥኩኝ እውነት ገደል ይግባ
 ዝምታ ነው መልሴ ፈትሕ ከተዛባ 
ለእውነት ተስፋ ቆረጥኩ 
መጥፎ ቦታ ወደቅኩ 
ሽንፈቴን ቀምሼ 
እራሴን ወቅሼ 
ትቢያ አመድ ለብሼ
 ወጣው ተዘረሬ 
በእራሴ መረብ ላይ ጎሉን አስቆጥሬ።

የጊዜ ጉዳይ ነው 
ላይነጋ መስሎ ቢጨልምም ፤
ተስፋህ ተሟጦ ያለቀ ቢመስልም ፤
የጠለቀች ፀሀይ ስጠብቃት ጠፍታ ፤
ለቅሶ ማታ ሆኖ ጠዋት እርቆ ጠፍቶ ደስታ፤
በችግር ላይ ችግር ቢደራረብብህ ፤
አለኝ ያልከው ሰውም ፊቱን ቢያዞርብህ፤
አንድ ነገር አድርግ ቀና በል ወደ ላይ፤
ተስፋን የሚቀጥል አለና በሰማይ፤
በፍፁም አትጉበጥ አትይ ወደ ምድር፤
የጊዜ ጉዳይ ነው ያልፋል ሁሉም ችግር::

~~የአዞ እንባ ~~(ሳሙኤል አዳነ)
ባልበሰለ አይምሮ 
ሀገር ልናቆስል ፣
ከራስ ጋር ተጣልተን 
ብሄር እንገምዳለን 
አዋቂ ይመስል ።
.
እምነት አለኝ የሚል 
መፆም ያላቃተው ፣
መነው ይችን ሀገር 
ካለችበት ፍዳ 
መታደግ አቃተዉ ።
.
ለካስ ውሸት ኖሯል 
ያዞ ነው እንባችን ፣
ከይቅርታ ጀርባ 
ከሳሽ ነው ልባችን ።
ፀሎት መፃፍ ይዘን 
ጦር አለ በጃችን ።
የይምሰል ለቅሷችን 
ግፍ እየቋጠረ ፣
ዞሮ እሚያቃጥለን 
አሲድ ሆኖ ቀረ ።
.
እባክህ አምላኬ 
ፅድቁም ይቅርና 
በቅጡ ኮንነን ፣
የአንድናት ልጆች 
ተባልተን እንዳናልቅ 

አስታራቂ ሆነን ።

➛➛ተፈጥሮን ደጅ ልጥና➛➛

" እኔ ልሙትልሽ" እያልኩኝ አልምልም
ቃላቴን መንዝሬ፣ለሞት ቀብድ አልከፍልም
ያኔ ትዝ ይልሻል?
"ራስህን ግደል" ብለሽ በረኪና የላክሽልኝ ጊዜ
እድሜ ለስጦታሽ፣ ታጠበ ሸሚዜ።

ገደብ ጫፍ በሌለው፣ በልቤ መጋዘን
ቢታጨቅ መከራ፣ ቢጠራቀም ሀዘን
"ባለፈልኝ" እንጂ "በሞትኩ" ብየ አላቅም
ካልጋ ላይ ነው እንጂ፣ ከፎቅ ላይ አልወድቅም።

በሀኪሙ ስተት ፣በቁሜ ብከፈን
በወርድ በቁመቴ፣ ሳጥኔ ቢደፈን
ከጭስ እቀጥናለሁ፣ እኔ መውጫ አላጣም
በጠጅ በወይን አገር፣ሽጉጤን አልጠጣም።

የተመደበልኝ ዘመን ከባከነ
የተሰፈረልኝ ፣ቀን አልቆ ከሆነ
ተፈጥሮን ደጅ ልጥና
ባዲስ መንገድ ትስራኝ፣ባዲስ የፍጥረት ውል
መስኮትሽ ላይ ሆና
ስትዘምር የምትውል
ድንቢጥ ወፍ ታድርገኝ
ብኖር አንቺን አየሁ፣ ከመሞት ምን ሊገኝ?

➛ገጣሚ ፦በእውቀቱ ስዩም

ስሚ!
እኔ በዚህ ዐለም ፤ብዙ ብሰቃይም
አንድ ሀሙስ የቀረው፤ መስየ ብታይም
አምሮቴን ሳላገኝ፤ሱሴን ሳላከትም
በመሬት ከርስ ውስጥ ፤ገላየን አልከትም
አልሞትም!

ማንም ባልደፈረው፤ መንገድ ሳልገሰግስ
እንደ ንጉስ አይዙር፤ግማሽ ቀን ሳልነግስ
በጠገበው ሳልስቅ፤ ለራበው ሳልደግስ
አልሞትም!

ዝማሜን ሳላወልቅ፤ ያንድበቴን ግድብ
ዙፋን ላይ ሳልሸና፤ ጌቶቼን ሳልሰድብ
ከድሃ ሳላብር፤ ከገባር ሳልወግን
ከምድር በረከት፤ ድርሻየን ሳልዘግን
አልሞትም፤
ስሚ!

ልቤ እንደምኞቱ፤ ቢያገኝ እንደምርጫው
ያላማየ ማብቂያ፤ አንቺ ነሽ መቁዋጫው
እና
አገሬን ለቅቄ፤ ልብሽህ ላይ ሳልከትም
በውብ ከንፈርሽ ላይ፤ ከንፈሬን ሳላትም
አልሞትም!

 ➢ገጣሚ ፦በእውቀቱ ስዩም 


➢➢ላ’ንዲት የገጠር ሴት➢➢

ስትፈጭ የኖረች ሴት፣
መጁ በመጠኗ፣ ወፍጮውም በልኳ፣
ጓያ ትፈጫለች
ጓያ ሽሮ ሲሆን ያበቃል ታሪኳ !!
   
አስባው አታውቅም…
ወደ ኦናው ምድር ለምን እንደመጣች፣
ከ’ለታት አንድ ቀን፣ ከና’ቷ ሆድ ወጣች፣
ከ’ለታት አንድ ቀን፣ ጡት አጎጠጎጠች፣
ከ’ለታት አንድ ቀን፣ ለባሏ ተሰጠች……

ተዚያን ቀን ጀምራ፣
ተዚያን ቀን ጀምሮ፣
ድንግል ድንጋይ ወቅራ፣
ትፈጫለች ሽሮ……

አታውቅም፣
ማን እንደሚባሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣
አታውቅም፣
ሹማምንት በ’ሷ ስም፣ ምን እንደሚሠሩ፣
አነሳኹት ‘ንጂ፣ እኔም ለነገሩ፣
ፖለቲካ ጥበብ ራስን ማራቀቅ፣
ምን ይጠቅማትና ጓያዋን ለማድቀቅ

ከቶ ማንም የለ, አበባ ‘ሚሰጣት፣
ከቶ ማንም የለ፣ ከተማ ‘ሚያወጣት፣
ከቶ ማንም የለ ፣ በዳንኪራ መላ፣ ወገቧን የሚያቅፋት፣
ልፋቷም፣ ዕረፍቷም፣
ወደዚህ መጅ መሳብ
ወደዚያ መጅ መግፋት……
እንደ ዓባይ ፏፏቴ፣
ሽህ ዓመት ቢንጣለል፣
ቢጎርፍም ዱቄቱ፣
እንደ ሲኦል ወለል፣ ጫፍ የለውም ቋቱ!
    
ከዘመናት ባንዱ
መስተዋት ፊት ቆማ፣ በተወለወለው፣
ራሷን ለማየት፣
ከጸጉራ ላይ ያለው
ዱቄት ይኹን ሽበት ሲያቅታት መለየት፣
ያኔ ይገባታል
የተሰጣት ዕጣ፣
ከማድቀቅ ቀጥሎ፣ መድቀቅ እንዲመጣ…
    
የመጅ አጋፋፏ - አምሳለ ሲሲፈስ፣
ከቋት ሥስት እንጅ፣ ሢሳይ አይታፈስ፣
ትቢያ ‘ሚተነብይ ዱቄት በዙሪያዋ፣
ከባርኔጣ አይሰፋም፣ የኑሮ ጣሪያዋ፣
"ስትፈጭ የኖረች ሴት"
ይህ ነው መጠሪያዋ! 

➛➛ገጣሚ ፦ በእውቀቱ ስዩም

​​┈◦◎●◉ አባ ይፍቱኝ◉●◎◦┈

ሲኦል አለ ሲሉኝ የለም ብዬ ክጄ
የባልቴት ተረት ነዉ በማለት ቀለጄ
አዉቄ በድፍረት በድያለሁና
ያንፁኝ በንስሀ ያንሱኝ በቀኖና
ሲኦል ከነ ጭፈራዉ በጉም ተሸፍኖ
እንዴት ሳላየዉ ኖርኩ ካጠገቤ ሆኖ
አባ ይፍቱኝ.
ሰይጣን ብሎ ነገር የተጭበረበረ
ዋዛ ነዉ ቧልት ነዉ ብዬ አስብ ነበረ
ይሄዉ እውነት ሆኖ ዋዛና ተረቱ ባይኔ በብረቱ
ዲያብሎስን አየሁት በጋቢ ተሸፍኖ ዘንጦ
እልፍ ግዳይ ጥሎ ቸብቸቦ ጨብጦ
አባ......
ልክ እንደ ብርሌ አጥን ሰክስ
አባይን አዋሽን የሚያስንቅ ደም ሲያፈስ
ለምለም ፍጥረት ሁላ ወደ አመድ ሲመልስ
ልክ እንደ ጧፍ ሀዉልት ምስኪኖች ሲጋዩ
ምድጃ ዳር ሆነዉ ይህንን እያዩ
አባ
ገሀነም ከላይ ነዉ ብለዉ በመሳሳቶዎ
እርሶ እንደፈቱኝ እግዚሀር ይፍታዎ
           
   ገጣሚ ፦ በእውቀቱ ስዩም

ሀሳቤና ኪሴ
ተበድሬ እጄም ባዶ ሆነ
አምላኬም ጨከነ
ሳይሰጥ ከሚነፍገኝ
ሠጥቶ ቢፈትነኝ
ምነኛ ደስ ባለኝ 
ይሰጠኛል ብዬ በሀሳብ ቤት ስሰራ
ላዬ ላይ ፈረሰ ...
ቁጭ. ብዬ ብቻ ሳልቆም ስንጠራራ
እንደ ሀሳቤ ምኞት ሳይሞላልኝ ኪሴ
ቀናቶች አለፉ ስትሳቀቅ ነፍሴ
እንዴት ረሳኸኝ ስምህን ስጠራ
ሆድ አስባስከኝ እኮ 
ያላንተ የት ልሂድ ማንንስ ልጣራ
ሲጠይቁህ እንደቸርካቸው ^^^    
ለኔም ቸረኝና ^^^^
በደስታ በሀሴት ልኑር እንደገና
እንደ ልቤ ልሁን ...  እንደገና
ከቤት ከጎረቤት ... 
የተበደርኩትን ሙሉ ልክፈልና
አደባባይ ልውጣ እፎይ ልበልና

ተማጥኖ ለገመድ
             (ልዑል ሀይሌ)

እንፈራገጣለሁ
ያሰረኝን ገመድ ታግዬ ለመፍታት፤
የማሠሪያ ዕጣ ነው
በነፃነቱ ልክ
እስረኛዋን ነፍሴን ነፃ የሚያወጣት፤
.
ነፃ ውጣ ገመዱ!
አትገደብ በኔ በገላዬ ልኬት፤
የኔ ስቃይ አይሁን
ያንተ ጥጋት ስኬት፤.
.
የውልህ ገመዴ!...
ኑሮን እወቅበት ክንድህን አበርታ፤
ስንት ልብስ መሰለህ
ታጥቦ ሚጠብቀው ከላይህ ሊሰጣ፤
ስንት ስጋ አለልህ
ቋንጣነትን ብሎ አንተን የሚማጠን፤
ሂድ መከታ ሁነው
እስራቴን ለቅቀህ
ጀግን በፍጥረትህ በመክሊትህ መጠን፤
.
የውልህ ገመዴ!...
አትያዘኝ ጨምድደህ አትፍቀድ እስራት፤
አሳሪውን ትተህ
ውስጥህን አድምጠው ፍርቱናህን ኑራት፤
.
ገመድ ሆይ ልቀቀኝ!!
አታብዛው ጭንቀቴን ነፃ ሁን ተፈታ፤
አንተም እስረኛ ነህ
ዕድሜህን ከፈጀህ
ለአሳሪው ትዕዛዝ ገላህ ከተረታ፤
ነፃ ሁን ገመዴ!!..

፯-፮-፳፻፲፩ ዓ.ም.


❤️ፍቅር ማለት ውዴ ❤️

ፍቅር ማለት ውዴ ፨
የህልሙ ዘራችን የዕውን ፍሬ አፍርቶ ፤
ቆንጅየ ልጅ ወልደን...
እሱም ፍቅር ሊማር አንደበት አውጥቶ ፤
ፍቅር ማለት.... እማ? ብሎ ቢጠይቅሽ ፤
ይህንን ንገሪው ሳትፈሪ ሳይጨንቅሽ ፤
........"ፍቅር ማለት ልጀ........
የተራ ሆሄያት ባዶ ጥርቃሚ ፤
የሶስት ፊደል ጥምረት የቀል ልቅምቃሚ ፤
የደቂቃ ስሜት.......
ወይ ጊዜያዊ ጥቅም አይደለም ምስጢሩ ፤
መስጠት+መስጠት +መሰጠት .....በቃ ሁሌም መስጠት
እናም ልጀ ይህ ነው የፍቅር ቀመሩ ፤...."
ብለሽ ንገሪልኝ እንዲገባው አርገሽ ፤
ፍቅርን ሠጥቶ .....
ምላሽ እንዳይጠብቅ በደንብ  አስጠንቅቀሽ ፤
...........ደግሞም እንዲህ በይው.........
......ፍቅር ማለት ልጀ...
በአንዲት ውብ ማሳ ውስጥ..
ከአረም ከቁጥቋጦ ፈፅሞ በራቀች ፤
ከአንድ ገበሬ እጅ..
በፅናት ተዘርታ በዕምነት የበቀለች ፤
........... .............ፍቅር ቡቃያ ነች ፤
የአለምን ሃይሎች አጣምሮ ያደላት ፤
የተንኮል ገሞራ .....
የሃሜት አውሎ ንፋስ ገፍትሮ ማይጥላት ፤
ገንዘብ ጎርፍ ሆኖ.....
ስሯን ቢያጥለቀልቅ ፈፅሞ ማይነቅላት ፤
ፍቅር ቡቃያ ናት..........."
......ብለሽ ንገሪልኝ....
ግን ይህን ሁሉ ቃል ከአንደበትሽ ሰምቶ ፤
....ፍቅር ማለት እማ ????
ብሎ ከጠየቀሽ ሳይረዳው ቀርቶ ፤
....ይህንን ንገሪው
"ገበሬው አምላክ ነው ማሳዋ ልባችን ፤
ዘሩ የፍቅር ቃል ቡቃያው ልጃችን ፤"
እንዲያውም እንዲያውም....
ከተራ ቃላት ጋር ምን አፈታተነን ፤
ፍቅር ማለት ውዴ!!!! በቃ እኔና አንች ነን ።

እንቁ
ከመስክ ወዲያ ማዶ ክፏፏቴዉ ክምር ከምንጩ  ሰፈፍታ
በእንስራ መልክህ ላይ ድንገት የፈሰስኩኝ የዉሃ ጠብታ
የምንጩ ቅዳሴ የኩለልታዉ ወረብ አንጀት እያራሰ መንፈስ እየረታ
የቀየዉ ዉብ ገንቦ እንዴት አፈቀረ የዉሃ ጠብታ
አንተ እንደዉ ግዴለህ
ወርቁ ለረከሰ የግብዛን ቅኔ መራድ አታዉቅበት
ወንጭፍም ጋሻ ነዉ ጠብታም ጸበል ነዉ አምኖ ላጌጠበት
ታማዉብሽ እቱ የምንጭ ላይ ሰፈፍ አንቺ ዉብ ጠብታ
እረሳሽዉ እንዴ የጎልያድን ትቢት ከአለታት በልጦ ጠጠር እንደረታ
ተርታ ናት ይሉኛል ዋጋሽን ተምነዉ በረከሰ ሚዛን
ለቃል ጦር አንወድቅም በደግነት ወንጭፍ ፍቅር ስለገዛን
ይኸዉ እንዲህ ሆነ
ከደብራችን ወዲያ ከድልድዩ ግድም  ማዶ ከገደሉ
የቀየዉ ዉብ ገንቦ በግብዞች ደንጋይ ተሰብረሃል አሉ
እኔማ ጠብታ ዉለዱልኝ ብዬ ከሰባሪህ  ችሎት ሰርክ እሞግታለዉ
ልፊ ቢለኝ እንጂ በአላዋቂ ሸንጎ ዳኛየን አይቸ ፍርዴን አዉቀዋለዉ
ተጥለሃል ቢሏት ከቆሸሳዉ ክምር ከድልድዩ ገደል
ድንግል ያልካት ምንጭህ ደፈረሰች ብለዉ ይነግሩሃል አደል
ዳርዳሩ እስክስታ ነዉ ጥግ ጥጉ እልልታ የዚህ ዘመን  ሙሾ
ምንጩ ምን በሰራ ደፈረስክ ይባላል እንስራዉ ቆሽሾ
ላላማረ መልኳ ምስኪኑ መስተዋት ለምን ይወቀሳል
እግር ለሸፈፈዉ ተሸካሚዉ ጫማ ለምን ይከሰሳል
በፈሪ ልቦና ወደቀሃል ወይ ሽሽት ውድቀት የጸነሰዉ ስበብ ይወለዳል
በጨቅላ መንገዱ በቋቋሙ ስቀዉ እንዴት ይራመዳል
ቀዳሽ በሌለበት ካህን በልዋለበት በተስኪያኑ ሞላ
ምን ይሉት መራመድ ተረከዝ ወደ ፊት እግር ወደ ኋላ
መቸም ወግ ነዉና ለነጠላዉ ዉበት ለቅዳሴዉ ክብር ከደብሩ ባይረቁም
እዉነት እልሃለዉ አማኝና ጌታዉ አይተዋወቁም
ጸጋዉ ባልጎደለ ባልጠገበች ምድር አራማጅ ቢከፋም
መንገድ በሆነ አለም ተራመጅ ልብ እንጂ ተጓዥ እግር አልጠፋም
እንዱህ ነዉ አለሜ
የፍቅራችን ቅኝት ዉሉ ሲደረደር በመኖር በገና
ሃገር እንስራ ነዉ ዉሃነት ህዝብ ነዉ ዘመን ጀርባ ሆና
ዘመን ጥያቄ ነዉ እንዴት ይሉት ስሌት ለምን ይሉት ቀመር
አስሞን ረክሶ ጀሮ ለምትለምን መላሽ ላጣች ሀገር
ዘመን ዝምታ ነዉ የፅሞና መንደር
የፈታትን አስራ ያኖራትን ገላ  በርባንን ለምትል የጲላጦስ ሀገር
እንዲህ ነዉ አለሜ
 በዘመን ክራር ላይ የግብራችን አዉታር ዉሉ ሲከረከር
ህዝብነት እነባ ነዉ ስንዴዋን በትና ዳቦ ለምትለምን  አመድ አፋሽ ሀገር
ሀገርማ በግ ናት የመጣ በሙሉ ስሞ የሚሸጣት የይሁዳ ጌታ
አራጅ እረኛዋን በእምነት የምትከተል ከገዳይዋ በረት ግልገሎቿን ትታ
ሀገር ሞኝ እናት ናት ከጠፈፈ ጡቷ ደም እየተለለ እስትንፋስ ገባሪ
መግል የያዘ ጡቷን ለነሽዋ ልካ ሞቶ አጥግቦ አዳሪ
እስኪ ልጠይቅህ ጣር ካመረቆዘ ከእንባ መቀነት ላይ ሳቅ ሰርቆ ማስካካት
ከፈን ከናፈቀዉ ከበረደዉ ገላ ሙቀት ሰርቆ መርካት
ችጋር ካቆረበዉ ከታጠፈ አንጀት ላይ ኩንታል ስጋ መብላት
ሸክም ከሞሸረዉ ከደቀቀ ወገብ ጉልበት ሰርቆ መርታት
እንዴት ነዉ እንኩዋንስ ጥም ገርፎት ከደረቀ ወዟ ጌጥ ሊርስ ለመጣ
እሷ የሰዉ ሀብታም ከአላምጠዉ ናፍቋት ታጎረሰዉ አታጣ
ብጣቂ ነጠላ ቅድ ነዉ ቀሚሷ
ጨቅይቶ ማድመቅ ነዉ መኖር ማለት ለሷ
ንገር ለሸማኔዉ በቀዳዳ ስበብ የቀሚስዋን ክብር ሊያስነዉር ቢለፋ
በጠማማ መድፌ በሰባራ ኪታን ሀገር አትሰፋም
እንስራየ እንዴት ነህ ሙሽራዬ እንዴት ነህ ኑሮ እንዴት ይዞሃል
 የጠብታ ፍቅር ከምን አደረሰህ ቅር ምንቅር አድረጎ ወይስ ወቶልሃል
እኔማ ጠብታ ዉለዱልኝ ብዬ ከሰባሪህ  ችሎት ሰርክ እሞግታለዉ
ልፊ ቢለኝ እንጂ በአላዋቂ ሸንጎ ዳኛየን አይቸ ፍርዴን አዉቀዋለዉ
እኔማ ጠብታ ይቅርብሽ ምኔ ነዉ በነጋ በመሸ  ዳናህን ናፋቂ
በተስፋ መንገድ ላይ ያልቀጠረቻትን ሀገሯን ጠባቂ
እጠብቃታለዉ ከዘመኔ መቅደስ እምነቷን አፅነቸ በቃል ኪዳን ፀበል
ከስር ካልጠመሙ መዝመም መዉደቅ አይደል
አውቃለሁኝ እኮ ተስፋ እየቀደሱ ያልቀጠሩትን ሰው  መጠበቅ ይደክማል
ልብ በል ወዳጄ አሰተዉሎ አሚያዘግም ከሚሮጥ ይቀድማል
በደልን ጠፍንገዉ በፍቅር ካልቀጡት
 እያደር ይገላል  ቂምን ፊት ከሰጡት
እንጂማ እናውቃለን እንደ ባሪያ በልቶ እንደ ንጉስ ማግሳት ሰባሪህ ቢመኝም
ከደቀቀ ወገብ ጉልበት ሰርቆ  መርታት ብልህ አያሰኝም
ገዝፎ ቢያንበረክክ የችጋርህ ቁና የመከራህ ኩንታል
ከመሮጥ አተቁም ሁሌም ከእንቅፋትህ እግርህ ይበረታል
አስተዉል ሰባሪ በተራራ ጉራ ሸለቆ ልብ ይዘህ በድፍረት አትዛት
የልቅ እድልህን በጥረትህ ተመን ከልብህ ላይ ግዛት
አሳር አደብ አይቶ መከራ የወለዳት ጀግና ናት አትክድም
በሸረበኞች ተረት በሽንታሞች ደንጋይ ሀገር አትናድም፡፡

ድሮ ድሮ 
ድሮ ድሮ ድሮ… ድንጋይ ዳቦ እያለ
ሰማይ እንደ ጣራ ሳይርቅ ዝቅ እንዳለ
ዶሮም እንደ አሞራ መብረር እየቻለ
ታስታውሺ ነበር እወድሽ ነበረ…
.
ታድያ ምን ያደርጋል ሁሉም ተቀየረ
ድንጋይ ዳቦ ትቶ ድንጋይ ሆኖ ቀረ
ሰማይ አፈንግጦ እንደዚህ ከፍ አለ
ዶሮም መብረር ትቶ መራመድ ጀመረ
ልቤ ግን ልብ ነው ያኔ እንደነበረ

በዘመኑ ሙሉ ሲያፈቅርሽ የኖረ።

ልጅት ምን ሆናለች ?
////////\\\\\\
መውደዴን ስነግራት ፣
ሳቅ ሲተናነቃት፡፡
‹‹አብረን እንሁን›› ስላት ፣
ሳቅ ሲተናነቃት ፡፡
‹‹አፈቀርኩሽ›› ስላት ፣
ሳቅ ሲተናነቃት ፡፡
መልሱን ስጠይቃት ፣
ሳቅ ሲተናነቃት ፡፡
‹‹ ላግባሽ ባልኳት›› ጊዜ ፣

ትንታ ገደላት ፡፡


ልረሳሽ ፈልጌ
መርሳቴ ተረስቶኝ ፣ ያው እንደፈራሁት
ስምህ ማነው ቢሉኝ
ስሜን እረስቼ ፣ ስምሽን ጠራሁት
ቱ ...
አንቺን ልረሳ ስል
አንቺን እያወሳሁ ፣ ስሚኝ ስቀባጥር
ለካስ ማስታወስ ነው 

የማይረሱትን ሰው ፣ ለመርሳት መሞከር ።


❤️❤️ማ ይንገርሽ😷😷


ብዙ አስብና ማፍቀሬን ልነግርሽ
መኖሬ ላንቺ ነው ወድሻለሁ ልልሽ

ግና ገና ሳይሽ

ያ ሁሉ ስቃየን አይደለም ልናገር
ላንቺ የሆንኩትን እንኳን ልመሰክር

ጉልበቴም ይዝላል  
አካሌም ይደክማል
ልሳኔም ይዘጋል 
ልቤም ያው ይፈራል

ታዲያ የኔ ፍቅር

የልቤን ፍላጎት አፌ ካላወራው
ፍቅርሽን መራቤን ልቤ ካላወጣው
ገና ሳይሽ አንቺን ጉልበቴ ከዛለ
አካል እስትንፋሴ ባንቺ ከተከለለ

ማን ይንገርሽ እና እንዴትስ ታቂያለሽ

እስከ ሞቴ ድረስ እኔ እንደምወድሽ

..ስርዝ ድልዝ ደብዳቤ
.
እዚ ደብዳቤ ላይ
ልነግርሽ ያሰብኩት
አስቤ የፃፍኩት
ፅፌ የሰረዝኩት
ሰርዤ የላኩት
ስርዝ ድልዝ ሆኖ አልነበብ ካለሽ
ሳልሰርዘው በፊት
ምን ይላል መሰለሽ…
.
መግቢያውም
መደምደምያው ሀተታው በሞላ

ሌላ አይናገርም

የኔ ቢጤ ለማኝ
መንገድ ይወስደኛል መንገድ ያመጣኛል 
እህ ስለው ደግሞ ጉድም ያሳየኛል
በዘመን ብራና በዘመኔ ብእር 
ችጋራም የሚል ቃል ተፅፎበት ነበር
አንጀት ከሚበላው ከዋሽንቱ ጀርባ
ከርሃብ ተወዳጅቶ ሆድን እያነባ
ዝናብና ምራቅ ከሚናፍቅ ከንፈር
ይታየኛል መጉደል በድሀ አፍ ሲነገር
በሊቃውንት ደጃፍ ሰርክ እየደገመ
በደከመ ትንፋሽ ዋሽንት እያዜመ
በማርያም እያለ እንዲህ እንደጎበጠ
የኔ ቢጤ ለማኝ በዛች አስር ሳንቲም ምርቃቱን ሸጠ
ያንተ ቢጤ መፅዋች ሳንቲሙ የበዛ
በዛች አስር ሳንቲም ገንዘብ ማይመልሰው ምርቃትን ገዛ
የኔ ቢጤ ለማኝ
በልብ ስርጣ ስርጥ ትንፋሽ እየማገ
ለብሶት የሚሆን ዜማ እየፈለገ
ደረት እየደቃ ላይን እየሳበ
ጆሮ የሚገባ ቃል አጥብቆ እያሰበ
መሔጃ ቢጠፋው ሰርክ እየቆዘመ
ሳንቲም ምን ያደርጋል ሆድ ካላከረመ
መንፈግ አጎብጦት እያሰላሰለ
ስለምን ይቦካል ጋግረን ካልበሰለ
በሚል ዜማ ቅኝት መፅዋች ይጣራሉ
ደሀን የዘረፉ በመራቡ ብዛት ስላዜመው ዜማ ያጨበጭባሉ
አድናቆት ምንድን ነው እንጀራ ይሆናል
ጭብጨባ ምንድነው ረሀብን ያስረሳል
ምንድን ነው ጭብጨባ
ሙሾ እየወረድን አይን እያነባ
የኔ ቢጤ ለማኝ አስፋልት ዳር ቆሞ ህዝብ ይለማመናል
ለጋሹም ሞኝ ነው ከሱ የዘረፈውን መልሶ እየሰጠ መፅዋች ይባላል
የኔ ቢጤ ለማኝ
በጎበጠ ገላ ማንከስ ተያይዞ
እግሮቹ ከድተውት እንጨት ተመርኩዞ
ይወድቃል ይነሳል ደግሞ ያደከድካል
ስለ እግዜር እያለ ደጄ ላይ ያለቅሳል
ቤተ መቅደስ ሔዶ ማረኝ እንዳይለው መግባት ተከልክሎ
ከሰውነት ወቶ ከሰው ተራ ጎሎ
አለም ከነ ለህዝቦ መኖሩን እረስታው
አጥሬን ተደግፎ በማርያም ይለኛል እንዳተልተጎዳ ሰው
ህዝቡ ተማረ እንጂ መቼም አይለወጥ
ጀግንነት መስሎታል
የወደቀን መጣል የጣለውን መርገጥ
የኔ ቢጤ ለማኝ ወድቆ የተረገጠ
ደሀ ነው ተብሎ ለሀብታም የተሸጠ
ሀብታሞቹም ጣሉት አይጠቅምም ተባለ
ይኸው ከዛ ወዲህ ሰፈሬን ይዞራል በማርያም እያለ
ጆሮ ለሰጠው ሰው ቀርቦ ለጠየቀው
መጣሉ አደለም ብሶት ነው ያጎበጠው
የኔ ቢጤ ለማኝ
ሀገሩ ላይ ከብሮ ቅኔ እየዘረፈ
ከብት እየጠበቀ ድርሳን እየፃፈ
ሀገሬው እንዳይራብ ያረሰው መሬት ላይ ዘር እየጨመረ
ለሀገር እያነጋ ለሀገር እያደረ
ከለመለመ መስክ ቀዬ እየመገበ
ከጥጃ ተሻምቶ ወተት እያለበ
ባእድ መጣ ሲባል ቀድሞ የደረሰ
በመራራ ትግል ድል እየሰለሰ
ቀዬ ያከበረው ባድባር የተፈራ
ለራበው ሚያበላ ለቸገረው ሚሰጥ በህግ የሚመራ
ያንን መሰል ጀግና ያንን መሰል ጎበዝ ችግር አጎብጦት
ስለእግዜር ይለኛል አጥሬን ተደግፎት
የኔ ቢጤ ለማኝ
ከጭብጥ መዳፉ ዳቦ ተሰርቆበት
ምርኩዝ የነበረው እንጨቱን ነጥቀውት
ኡ.ኡ.ታ ያሰማል ጩኸት ይደመጣል ከነተበ አንደበት
ህልሙን ቅዠት አርገው እየመለሱለት
እየተንፎቀቀ የዳዊት መፅሀፉን ባንገቱ አንዳዘለ
መንደሬን ይዞራል በማርያም እያለ
ከጎደለ ገላ ሞትን ከሚፈራ
እንዴት ያስለቅሳል በደረቀ ከንፈር ማርያም ስትጠራ
መንደሬን ይዞራል
ብሶት የወለደው ዜማ እያዜመ
አንጀት የሚበላ ቃል እየቀመመ
መንደሬን ይዞራል
እንባውን እያየሁ እንባዬ ጠፍቶኛል
ብሶቱን ስሰማ ችግሬ ከድቶኛል
የኔ ቢጤ ለማኝ
በማርያም እያለ መንደሬን ይዞራል
መንደርተኛው ወቶ ማርያም ትስጥህ ይላል
እግር አጥቦ ስሞ ያበላ የነበር
ያ ብርቱ ገበሬ ያ ጀግና ወታደር
መሬቱ ተነጥቆ ዳቦውን ተሰርቆ ልብሶቹ ተገፎ
ስለ እግዜር ይለኛል በማርያም ይለኛል አጥሬን ተደግፎ
በአራት ሰፌድ እንጀራ ቆልሎ
አልጋገርንም ይላል በመቤቴ ምሎ
ሞልቶ ለሚተርፍ ሻግቶ ለሚደፋ
በማርያም እያለ የሚሰጥ ሰው ጠፋ
ምን አልባን ምን አልባት
ከመቶ ሚሊዬን ምን አልባን ምን አልባት አንድ ሰው ከሰጠ
እሱም ይነጠቃል እየተረገጠ
የኔ ቢጤ ለማኝ
ስለ እግዜር እያለ ሰው ይለማመናል
መስጠት እማይፈልግ እግዜር ይስጥህ ይላል
እግዜር መስጠት ትቶል
ታድያ ማን ይሰጣል


ጥርሴ!!
የውስጤን ደብቄ እንዳልተከፋ ሰው
ጥርሴ ፍልቅልቁን ገለጥ ሳደርገው
የራሴ አካል ሆኖ የራሴ ወገን
መግለፅ ያቅተዋል የልብ የሀሳቤን
እኔ ልዘን እንጂ እሱማ ምን ገዶት
ማንስ ሊያዘው ያሻል ወግድ ለማለት
አካሌን ስሰይም ከበደኝ እኔን
ታዲያ ምን ልበለው ይሄንን ጥርሴን?
እኔ ሳዝን አዝኖ፣ እሱ ካላዘነ
ምኑን ምን ሆነና የግሌ አካል ሆነ!


‹እሮጣለሁ›››
መድረሻ የሌለው፣
ዳና ተከትዬ ፣ ላልደርስ ከዳርቻ
መኳተን ብቻ ነው፣ 
የኛ ዕድል ፈንታ ፣ እስከ እድሜ መባቻ፡፡

እሮጣለሁ
አዲስ ነገር ላይወርድ፣
እርም ያለ ይመስል ፣ ፈጣሪ ጨክኖ
በዘልመድ ጉዞ ፣ በጠባቧ መስኖ፤
መፍሰስ ሲያወርሰው ፣ ላልታደለው እግሬ
ቃሉን ተቀበዬ
ለፍለጋው ልባክን ፣ ቢባረክ ዘመኔን፡፡
እሮጣለሁ
ያደረግኩት ጫማ ፣ እስኪንሻፈፍ ድረስ
እስካሁን ባይቀናው ፣ ዳርቻ ለመድረስ፤
ብቻ እዞራለሁ፣
ፍለጋ አንድ ነገር ፣ በማይገባኝ ምስጠት
ነፍሴ ብትፈወስ፣
ከሱ ተቀብዬ ፣ መሻቷን ለመሙላት፡፡
ይኸው ነው ዓለሜ፣
ካለመጓዝ በቀር ፣ ሌላ ዓለም የለኝም
ከዳርቻ እስክደርስ ፣ ለሰከንድ አልቆምም፡፡
እሮጣለሁ፡፡

እይውልሽ ውዴ !!!

" መንገድ አይኑ ይፍሰስ አይባልም ደርሶ
የወሰደውን ሰው ያመጣል መልሶ "
ሲሉ ብሰማቸው
ሲሉ ባደምጣቸው
ሁሉን ነገር ትቸ
መንገድ ላይ ተኝቸ
አንችን እየጠበኩ
አንችኑ እያለምኩ
ቀኑ መሽቶ ነግቱዋል
አመታት አለፍዋል
እልፍ አእላፍ ሌሊት
ዘመን ተቆጥረዋል
ግና ውዴ
አንች የለሽም ብየ
አልመጣሽም ብየ
እቤቴ ገብቼ
አንቺን ረስቼ
እንደገና ዳግም
ፍቅርን ከማልም
አዲስ ከመላመድ
ከሌላ መዛመድ
አንችን አስወጥቼ
ሌላ ሰው ተክቼ
መኖርን አልችልምና
ዛሬም እንደገና
አንች ቀረሽ ብየ እቤት ከምገባ
አንች የለሽም ብየ ሌላ ከማስገባ
የወሰደሽ እግርሽ
አዙሮ. እስኪያደርስሽ
የወሰደሽ መንገድ መልሶ እስኪያመጣሽ
እጠብቅሻለሁ ለምን አልጠብቅሽ !!!






No comments:

Post a Comment